Telegram Group Search
† ስንክሳር ሐምሌ 8 †

እንኳን ለቅዱሳን ጻድቃን ወከዋክብተ ገዳም አቡነ ኪሮስ: አባ ብሶይ እና አባ ሚሳኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

🔔††† አቡነ ኪሮስ ጻድቅ †††🔔

የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው: ክቡር ነው:: በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል::

አቡነ_ኪሮስ የተወለዱት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው:: ተወልደው ባደጉባት ሃገር #ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል:: ወንድማቸው (ታላቁ #ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግስቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው: አሕጉር አቋርጠው ወደ ግብፅ ( #ገዳመ_አስቄጥስ) መጡ::

እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም:: ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ ገብረ_ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ:: "የቅኖች ትውልድ ይባረካል" እንዳለ #ቅዱስ_ዳዊት:: አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው:: አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ #አቡነ_በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል::

ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ:: "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለ40 ዓመታት አልቅሰዋል:: በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል:: ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል:: አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል::

አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ:: ሱባዔ ገብተው: ፍጹም አልቅሰው: ከጌታም አማልደው: የዛን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም ባንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ::

ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት አልቅሰው: ሙታኑን አስነስተው: ንስሃ ሰጥተው: ገዳሙን የጻድቃን: ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል:: ጻድቁ #እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በስዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር:: እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር::

ከዚህ በሁዋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለ57 ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ:: ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና) በየቀኑ ይጐበኛቸው: ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ጌታ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን: ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ::

#ቅዱስ_ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው: በበገናው እየደረደረላቸው: ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ጌታችንም ታቅፎ: ስሞ ይዟቸው አረገ:: ሥጋቸውን #አባ_ባውማ ቀበሩት:: የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ: ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር:: እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም::

† የበርሃው ኮከብ አባ ብሶይ †

ታላቁ አባ ብሶይ (ቢሾይ):-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ
¤በመላእክት መሪነት የመነኑ
¤የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ባልንጀራ
¤የአባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር የነበሩ
¤በአጭር ጊዜ የብዙዎች አባት የሆኑ ሰው ናቸው::

††† እንቅልፍን የማያውቁ
¤በ40 ቀን ብቻ እህል የሚቀምሱ
¤የጌታችንን እግር በየቀኑ እያጠቡ የሚመገቡ
¤ፈጣሪያቸውን በጀርባቸው ያዘሉ (ነዳይ መስሎ አግኝተውት)
¤በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጉ
¤በርካታ ጻድቃንን የወለዱ ታላቅ የፍቅር ሰው ናቸው::

በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሰርተው: ቤተ_ክርሰቲያንን በንጽሕናቸው አስደስተው: ሐምሌ 8 ቀን ዐርፈዋል:: ግብፅ ውስጥ የሚገኘው ገዳማቸው ዛሬም ቤተ አበው: ተአምራት የማይለዩትና ተወዳጅ ነው:: ቦታው #መካነ_ሱባዔ_ወመንክራት ነውና::

🕊† አባ ሚሳኤል ነዳይ †🕊

መቼም ያ ዘመን (4ኛውና 5ኛው ክ/ዘመን) እጅግ የተባረከ ነው:: ቅዱሳኑ በብዛት የባለጸጐችና የነገሥታት ልጆች ናቸው:: አባ ሚሳኤልም የኬልቄዶን ንጉሥ ልጅ ሳሉ መንነው በበርሃ ለ65 ዓመታት ተጋድለዋል:: በመጨረሻ ግን በደዌ ምክንያት ወደቁ:: ለ5 ዓመታት መነኮሳቱ ሲጠይቁዋቸው ቆይተው ሰለቹ::

ከዛም ለ15 ዓመታት ላበታቸው በግንባራቸው እየተቀዳ: ያለ ምንም ምግብ እያቃሰቱ በበዓታቸው ወድቀው ኑረዋል:: ቸሩ አምላክ ግን 4ቱን ሊቃነ መላእክት ( #ሚካኤል: #ገብርኤል: #ሩፋኤልና #ሳቁኤልን) አዞላቸው ሲጠብቁዋቸው ኑረዋል::

በዚህች ቀንም #አቡነ_ኪሮስ መጥተው አጽናንተው: ጌታችንንም ጠርተው እንዲያርፉ አድርገዋል:: መላእክት እያጠኑና እየዘመሩ ጻድቁ ቀብረዋቸዋል:: በመቃብራቸውም ላይ ፈውስ የሆነ ጸበል ፈልቁዋል::

እግዚአብሔር የእኛን ያይደለ የጻድቃኑን ቅድስና አስቦ ይራራልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

ሐምሌ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ኪሮስ ጻድቅ (አረጋዊና ገዳማዊ)
2.አባ ብሶይ ጻድቅ (ኮከበ ገዳም)
3.አባ ሚሳኤል ነዳይ (ጻድቅ)
4.አባ ቢማ ሰማዕት
5.አባ በላኒ ሰማዕት
6.ቅዱሳን አቤሮንና አቶም (ሰማዕታት)

ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
4.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

"በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው:: የኃጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሠቢያ ለበረከት ነው::" (ምሳ. 10:7)

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" (መዝ. 36:28-31)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
+ ማርያማዊ ደስታ +

ድንግል ማርያም ‘መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል’ አለች፡፡ የድንግሊቱን ጥበብ ተመልከቱ፡፡ ‘በመልአክ በመመስገኔ ደስ ይለኛል ፣ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች በመባሌ ደስ ይለኛል ፣ አምላክን ለመውለድ በመመረጤ ደስ ይለኛል’ አላለችም፡፡ የእርስዋ የደስታ ምንጭ ከእግዚአብሔር የተሠጣት ነገር ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

እግዚአብሔር የደስታህ ምንጭ ከሆነ በሕይወትህ ምንም ነገር ቢከሰት ደስታህን አይነካብህም፡፡ ድንግሊቱ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች በመሆንዋ ደስ ያላት ብትሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ ከሴቶች ሁሉ የተንከራተተች ፣ ከሴቶች ሁሉ ያዘነች ፣ ከሴቶች ሁሉ በዲያብሎስና ጭፍሮቹ የተጠላች ፣ በሔሮድስ በአይሁድ የተነቀፈች መሆንዋን ስታይ ደስታዋ በጠፋ ነበር፡፡

እርስዋ ግን ደስታዋ የመነጨው ከአምላክዋ ብቻ ነበር፡፡ ፍጹም የሆነ ውስጣዊ ደስታን ማግኘት የሰው ልጅ ትልቅ ምኞቱ ነው፡፡ ሰዎች ደስታን ፍለጋ ብዙ ይደክማሉ፡፡ ድንግሊቱ ግን የደስታ ሁሉ ምንጭ የሆነው አምላክ ከእርስዋ ጋር ነውና በፍጹም ደስታ ደስ ይላታል፡፡ የድንግል ማርያም ደስታ ልጅዋ ‘ደስታችሁን የሚወስድባችሁ የለም’ ያለው ዓይነት ደስታ ነበር፡፡ ዮሐ. ፲፮፥፳፪

‘ተፈሥሒ ፍስሕት’ (ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ) ፤ ሙኃዘ
ፍሥሓ (የደስታ መፍሰሻ ሆይ) ብለን የምናመሰግናት እመቤታችን ከማንም የሚበልጥ ደስታ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፡፡ ደስተኛ የነበረችው በምድር በነበራት ቆይታ የሚያስደስት ኑሮ ስለነበራት አይደለም፡፡ እንደ እርስዋ የተሰደደ ፣ ያለቀሰ ፣ የተጨነቀ ፍጡር የለም፡፡ እንደ ክርስቶስ መከራ የተቀበለ እንደሌለ እንደ ድንግል ማርያምም ያዘነ የለም፡፡ እርስዋ ግን ለሌሎች የሚተርፍ ወደ ኤልሳቤጥ የሚሸጋገር ፣ ሆድ ውስጥ ወዳለ
ፅንስ የሚጋባ ጥልቅ ደስታ ነበራት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‘ተፈሢሓ በነፍሳ  ፆረቶ በከርሣ’ ‘በነፍስዋ ደስ ተሰኝታ በሆድዋ ተሸከመችው’ እንዳለ እርስዋ የተደሰተችው ሥጋዊ ደስታን አልነበረም፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ገብርኤል )ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ደስታ ነውና ቅድስቲቱ ማንም ጋር ያልነበረ ደስታ ነበራት፡፡ ገላ. ፭፥፳፪

በእርግጥም ደስታን ወልዳ ደስ ባይላት ይደንቅ ነበር፡፡ እርስዋ የወለደችው ‘የመላእክት ተድላ ደስታቸው’ ነው ፤ እርስዋ የወለደችው መወለዱ ‘ለሰው ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች’ የሚሆን ልጅን አይደለምን?

እግዚአብሔር አብ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው’ ያለውን አንድያ ልጁን ልጅዋ እንዲሆን ሠጥቶአታልና እርስዋም በምትወደው በልጅዋ ደስ ይላታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‘ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ’ ካለ እግዚአብሔር የዘጠኝ ወር ቤቱ አድርጎ ያደረባት ድንግል ምንኛ ደስ ይላት ይሆን? መወለዱ ሰውና መላእክትን በደስታ እንዲዘምሩ ካደረገ የወለደችው ድንግል ምንኛ ደስ ይላት ይሆን?

ጌታ ለሐዋርያቱ ‘ስማችሁ በሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ’ ካላቸው እግዚአብሔር ሁለተኛ ሰማዩ አድርጎ ዙፋን ያደረጋት በምድር ያለች የጠፈር ባልንጀራ ፣ የአርያም እኅት ማርያም ምንኛ ደስ ይላት ይሆን?

እመቤታችን ሆይ እባክሽን በአንቺ ላይ ከፈሰሰው ደስታ ቀድተሽ ወደ እኛ ወደ ኀዘንተኞቹ አፍስሺ፡፡ ኖኅ እንደ ላካት ርግብ የመከራችን ውኃ ጎደለ ብለሽ ታበሥሪን ዘንድ ወደ እኛ ነይ ‘ንዒ ርግብየ ትናዝዝኒ ኀዘነ ልብየ’ ‘ርግቤ ሆይ ከኀዘኔ ታረጋጊኝ ዘንድ ነይ’ እንዳለ ሊቁ፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ነሐሴ 7 2015 ዓ.ም.
ለበዓለ ጽንሰታ ዝክር
ከብርሃን እናት ገጾች የተቆረሰ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
✝️✝️✝️ ነሐሴ 10 ✝️✝️✝️
††† እንኳን ለታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

✝️✝️✝️በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

✝️✝️✝️ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ
††† አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ:: አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው:: ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው::

ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ (ደብረ በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል::

በገዳሙ በጾም: በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል:: በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር::

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል:: ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ:: ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው::

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ:: ቀኑ ነሐሴ 10 ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ:: ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ::

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ:: ይሕን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል:: ይሕም ዘወትር ነሐሴ 10 ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል::

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ:: ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች:: ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ: እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት:: ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ:: በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ: በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም:: በሰማይም እሳትን አያዩም:: ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም::" ብሏቸው አርጓል::

ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተንቤን ተመልሰዋል:: ይሔው እኛ ምን ብንከፋ: ጻድቁንም ብንረሳቸው እግዚአብሔር ግን ዛሬም በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል:: ነገን ደግሞ እርሱ ያውቃል:: ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ (ጎንደር ቀበሌ 09 ኪዳነ ምሕረት) ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው:: ወርኀዊ በዓላቸው (በ19) ዓመታዊ በዓላቸው (ግንቦት 19, ነሐሴ 10) ነው፡፡

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው: ሦስት ሙታንን አስነስተው: ብዙ ድውያንን ፈውሰው: ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው: የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው: በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት 19 ቀን አርፈዋል:: የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው::

ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት: አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው: ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል::
በረከታቸው ይደርብን::

††† ✝️✝️✝️ቅዱስ መጥራ ሰማዕት †††✝️✝️✝️

††† ቅዱሱ በዘመነ ሰማዕታት በድፍረቱ ይታወቅ ነበር:: "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" እያሉ ሲያስቸግሯቸው በሌሊት ወደ ቤተ ጣዖቱ ገብቶ የአጵሎንን (የጣዖት ስም ነው) ቀኝ እጁን ገንጥሎ: (ወርቅ ነውና) ለነዳያን መጽውቶታል:: አሕዛብ በዚህ ተበሳጭተው በብዙ ስቃይ ገድለውታል::

†††✝️✝️✝️ ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት✝️✝️✝️ †††

††† በወጣትነቱ መከራን ሲቀበል አሕዛብ ሊያስቱት ሁለት ዘማ ሴቶችን ላኩበት:: እርሱ ግን አስተምሮ ክርስቲያን አደረጋቸው:: ለሰማዕትነትም በቁ:: በየጊዜው ሲያሰቃዩት ብዙ ተአምራትን ይሠራ ነበርና ከሰላሳ ሺ በላይ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል::

††† አምላካችን በወዳጆቹ ምልጃ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይሠውርልን::
አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፍቅርና በረከት ያብዛልን::

††† ነሐሴ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዓቢየ እግዚእ ኢትዮጵያዊ (ተአምራትን ያደረጉበት)
2.ቅዱስ መጥራ ሰማዕት
3.ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት
4.ሰላሳ ሺ ሰማዕታት (የሐርስጥፎሮስ ማኅበር)
5.ቅዱሳን ቢካቦስና ዮሐንስ (ሰማዕታት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
7.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

††† " ኑ የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ እዩ::
ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው::
ባሕርን የብስ አደረጋት::
ወንዙንም በእግር ተሻገሩ::
በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል::
በኃይሉ ለዘለዓለም ይገዛል::" †††
(መዝ. ፷፭፥፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
''እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተመሰገነ እወቁ'' መዝ ፬:፫

"እንደ ጽናጽልና እንደ መሰንቆ ድምጽ ደስ ለሚያሰኘው ቃልሽ ሰላም እላለሁ። ቅድስት ሐና ሆይ በቃልኪዳንሽ የመንግስተ ሰማያት በር አንቺ ነሽ እና ፊቱ የጠቆረ የአመፃ መላክ ሰይጣን በቅናት እንዳይዘጋብኝ ወደ እሱ እገባ ዘንድ በቃልኪዳንሽ ክፈችልኝ።"

        መልክዐ_ሐና




🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯
  ደብረ ታቦር 

➣ቡሄ ማለት ምን ማለት ነው?
➣ችቦ በቤተ ክርስቲያን እይታ ?  
➣ጅራፍ ማጮህ ምስጢሩ ምንድን ነው ?
➣ሙልሙል በቤተክርስቲያን አንድምታ እንዴት ይታደላል?

  🕯... እግዚአብሔር አምላክ ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጥልን !!!

       ።።።።። መልካም 🕯 ንባብ።።።።።

➣ ቡሄ

ቡሄ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን እና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል ይሰኛል ፡፡ አንድም ደግሞ ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን የሚገለጥበት ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡
አበው እንዲህ ሲሉ ወቅቱን ያመላሉ......
“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡

➣ ጅራፍ 

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር፤ በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ(መጥለፍ) እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር የያዘ ትውፊታዊ ተግባር ነው ...

1ኛ... ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡
2ኛ.... አንድም ደግሞ ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡

➣ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡  በምሽት ለምን ይበራል ቢሉ በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ አንድም ደግሞ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን መከራ እየተቀበለም አርአያ አንድም ምሳሌ ብርሃን መሆኑን አንድም በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡  ችቦውም በ12 ምሽት ይበራል ብርሃኑ የተገለጠው በዚችው ዕለት ነውና ፡፡

➣ ሙልሙል

በዚህች እለት በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን * ቡሄ * እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ይህን ማድረጉ ትውፊታዊ ብቻ አይደለም እንደ መጽሐፈ ቅዱስ  ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱ ሁሉ ልጆችም ዘምረው አመስግነው መርቀው ይሄዳሉና የዚህ ምሳሌ ነው።

ስብሐት ለእግዚአብሔር !
በዓለ ደብረ ታቦር

ክፍል አንድ


ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት በመሆኑ በየዓመቱ  በድምቀት ይከበራል፡፡ (ማቴ .፲፯፡፩፣ ማር.፱፡፩፣ሉቃ.፱፡፳፰)፡፡

ደብረ ታቦር፡- ‹‹ደብረ ታቦር›› ደብር እና ታቦር ከሚባሉ ከሁለት ቃላት የተገኘ ሲሆን ‹‹ደብር›› ማለት ተራራ ማለት ነው፤ ‹‹ታቦር›› ደግሞ በናዝሬት አካባቢ በሰማርያ አውራጃ በገሊላ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም ነው፡፡ የደብረ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል ፲ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ  ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ ፭፻፸፪ ሜትር ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ (መዝ. ፹፰፥፲፪) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጡ የነቢያት ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሳራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነበር፡፡ (መሳ. ፬፥፮)፡፡ የዚህም ታሪክ ምሳሌነቱ ባርቅ የጌታችን ሲሳራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል (፩ኛ ሳሙ.፲፡፫)፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ ያዩ ሲሆን አባታችን ኖኅ ይህንን ተራራ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡
የሐዲስ ኪዳን ወንጌል ጸሓፊያን ግን ‹‹ረጅም ተራራ፣ ቅዱስ ተራራ›› በማለት ጠርተውታል፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፣ በትውፊትም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፍሮታል፡፡

በዚህ በዓል አምላክነት፣ ጌትነት፣ ንግሥና የባሕርይ ገንዘቡ መሆኑን፣ የድኅነታችን መሠረቱም የጌታችን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆን (የተዋሕዶ ምሥጢርን)  የገለጸበት በዓል ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር/ እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፣ በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ” (መዝ.፸፪፡፲፪) በማለት ትንቢት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ማእከለ ምድር በተባለች በቀራንዮ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ቤዛነት ዓለሙን ሁሉ አድኗልና፡፡ ሆኖም ግን የጌታችን ነገረ ተዋሕዶ ምሥጢር በሥጋዊ ዕይታ ውስጥ ለሆኑት ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡

ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበት  ምሥጢር፡-

ሦስቱ ሐዋርያት በተራራው ሳሉ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ ይህ የብርሃነ መለኮቱ የመገለጥ የተዋሕዶ ምሥጢር እንጂ ውላጤ/መለወጥ/ አይደለም፡፡ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዲል፡፡(ሚል ፫፥፮)፡፡ ሦስት ክንድ ከስንዝር አካል ምሉዕ ብርሃን ሆኗል፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደ በረድ ጸዓዳ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ነገረ ተዋሕዶን እንዲረዱ የተደረገ የተዋሕዶ ምሥጢር ነው፡፡ ሰውነቱን ባይክዱም አምላክነቱን ግን ተጠራጥረው ስለነበር እነር በሚያውቁት በባሕርየ ትስብዕቱ አምላክነቱን ከሰውነቱ አዋሕዶ ምሥጠረ ተዋሕዶን ገለጠላቸው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ፴፪ ዓመት ከ፮ ወር ከ፲፫ ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል፡፡

ሙሴንና ኤልያስን በደብረ ታቦር ለምን አመጣቸው?

ሙሴን ከመቃብር ጠርቶ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት ጌታችን አምለካችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን የሰጠው ምስክርነት፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፣ውኃ ከዓለት ላይ ባፈልቅም፣ በዓመደ ደመና ዕብራውያንን እየመራሁ ጠላትን ድል ባደርግም፣ ደመና ብጋርድም፣መና ከደመና ባወርድም በአንተ መልካም ፈቃድ ነው፤ ብዙ ተአምራንት እንዳደርግ የረዳኝን የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ነው ይሉሃል? የሙሴ አምላክ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ሲል ኤልያስም ደግሞ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” በማለት የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ ሙሴና ኤልያስ የተጠሩበት ሌላው ምሥጢር ሙሴ “ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴን ግን አይታይም” ተብሎ ስለነበር (ዘፀ.፴፫፡፳፫) ከሞትም ከብዙ ዘመናት በኋላ ተነሥቶ ጌታን በአካል የማየትና ምስክርንት የመስጠት የቃል ኪዳን ተስፋ መፈጸሙን፣ ኤልያስም “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ሲሆን ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስን ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን ወደ ድበረ ታቦር አምጥቷቸዋል፡፡

መድኃኒታችን ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን “መነይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለ እምሕያው፤ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል? ብሎ ጥየቋቸው ነበርመና ሲመልሱ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› ብለውት ነበርና (ማቴ.፲፮፡፲፬)፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ‹‹በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር›› ያለውም የነበራቸውን ክብር ታላቅነት ያስረዳል፡፡

በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ሆኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ሆኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር (ዘፀ. ፴፫፡፲፫-፳፫)፡፡ ይህም በፊት የሚሄድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም አምላክ ሰው ሆኖ ሥጋን ተዋሕዶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” የተባለው ትንቢትም በዚህች ዕለት ተፈጸመ፡፡

ይቀጥላል...
📜 "የምወደው ልጄ ይህ ነው" 📜

ጌታችን ከሐዋርያቱ መካከል "አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንም" ወደ ቅዱሱ የታቦር ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።(ገላ 2፥9) ከተራራውም ጫፍ ሲደርሱ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የመምህራቸው ፊት እንደ ፀሐይ ሲያበራ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሲሆን ተመለከቱ። እነሆም ከቀደሙት ጻድቃን ታላላቆቹ ሙሴና ኤልያስ በታቦር ተገኝተው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

እነዚህ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ምን ተነጋገሩ? መቼም በጊዜው ከጌታ ጋር ውለው ያድሩ እንደ ነበሩት ተማሪዎቹ ሐዋርያት "አትሙትብን" አይሉትም። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሱባኤ የያዙለትና ደጅ የጠኑት የድኅነት ተስፋ እናዳይፈጸም "ይቅር አትሙት" እንዴት ይላሉ? ስለዚህ ከብሔረ ሕያዋን የመጣው ኤልያስና ከብሔረ ሙታን የመጣው ሙሴ በአንድ ላይ "በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለ መውጣቱ (ስለ መከራው፣ ሞቱ)" ያነጋግሩት ነበር።(ሉቃ 9፥31)

በታቦር ተራራ ላይ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መልእክተኞች ተገናኙ። በባሕር ላይ በእግሩ የተራመደው ጴጥሮስ፣ የኤርትራን ባሕር እጁን ዘርግቶ የከፈለው ሙሴን አየው።(ማቴ 14፥29፣ ዘጸአ 14፥21) የሰማርያ ሰዎች በተቃወሙ ጊዜ "እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው" ያሉ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ከሰማይ እሳት አዝንሞ ሃምሳ አንዱን ወታደሮች ያስበላ ኤልያስን ተመለከቱት።(ሉቃ 9፥54፣ 2ኛ ነገ 1፥10)

ሁለቱ ምስክሮች እንደ ተሰወሩም ወዲያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ዳሶች እንሥራ ብሎ ጌታውን ጠየቀ። ሐዋርያው በዚህ ተራራ ላይ መቅረት የፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። መድኃኒታችን አስቀድሞ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ዘንድ ብዙ መከራ ይቀበልና ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲነግራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ "አይሁንብህ፤ አይድረስብህ" ሲል ሊከላከለው ሞክሮ ነበር። ለዚህም በጊዜ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል" ተብሎ ተገስጾበታል።(ማር 9፥31-33) ይሁን እንጂ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ ያለውን ሁሉ እድል ተጠቅሞ ጌታን ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድና በካህናት አለቆች እጅ ተላልፎ ከመሰጠት ማስቀረት ስለሚፈልግ "ጌታ ሆይ፦ በዚህ(በታቦር ተራራ) መሆን ለእኛ መልካም ነው" ብሎ ተናገረ።

እርሱም ይህን ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። ከደመናው "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ መጣ። ሐዋርያቱ ይህን ድምጽ የሰሙት ሙሴ እና ኤልያስ ከክርስቶስ ተለይተው ከሄዱ፣ እነርሱም ወድቀው ከነበሩበት ከተነሡ በኋላ ነው። ይህም ከደመናው ውስጥ ሲወጣ ስለ ሰሙት ቃል "ለማን የተነገረ ይሆን?" ብለው እንዳይጠይቁና ምስክርነቱ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ እንዲረዱ ነው። በዚሁም ላይ ደመናው ወርዶ የጋረደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያቱንም ጭምር ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን ደመናው ጌታን ብቻ ጋርዶት ቢሆን ኖሮ፣ ሐዋርያቱ "እርሱን ስሙት" የሚለውን ቃል ራሱ ክርስቶስ ለራሱ የተናገረው ሊመስላቸው በቻለ ነበር።

ቅዱስ ጴጥሮስ "አትሙት" ያለው መምህሩን በፍጹም ልቡ ስለሚወደው መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ጴጥሮስ ጌታን የቱንም ያህል ቢወደው፣ ፍቅሩ ግን ከወለደው ከባሕርይ አባቱ ከአብ አይደለም ሊበልጥ ሊነጻጸርም አይችልም። ታዲያ አብ በእርሱ ደስ የሚለው፣ የሚወደው፣ አንድያ ልጁ እንዲሞት ፈቃዱ ከሆነ፣ የአብን ያህል ሊወደው የማችለው አረጋዊው ጴጥሮስ ለምን "አትሙት" እያለ ይቃወማል?!

አብ ምትክ የሌለው ልጁ ወልድ ሰው ሆኖ በክፉዎች እጅ ሲንገላታ እና እስከ መስቀል ሞት ሲደርስ እያየ ዝም ያለው ስለማይወደው አይደለም። ዓለም ያለ ልጁ መከራና ሞት ስለማትድን ነው እንጂ። ከዚህ ምን እንማራለን? ዛሬም ወደ መከራ የምንገባ የጸጋ ልጆቹ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች "እግዚአብሔር እንዲህ ስሆን ዝም ያለኝ ስለማይወደኝ ነው" አንበል። ባገኘን ጥቂት የሥጋ መከራና ሕመም የሚበልጠውን የነፍስ ጤና የምንሸምት ከሆነ እግዚአብሔር ዝም ይላል። ዝም የሚለው መከራችንን ስለማያይ ሳይሆን ከመከራው ጀርባ ያለው ዓላማ ታላቅና የተቀደሰ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ ነው።

ስብሐት ለእግዚአብሔር !
+ ኪዳነ አምላክ ማርያም ተስፋ መድኃኒት ዘዓርብ +

🎉🎉🎉 እንኳን አደረሳችሁ 🎉🎉🎉
📜


ዘከመ : አሃዘ : እግዚእነ : እዴሃ : ለእሙ : ዘየማን
ሃባ : ኪዳነ : ወመሐለ: ላቲ።



📜
+ እረፍተ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ድንግል ማርያም +
📜📖 📜📖 📜📖 📜📖 📜📖 📜📖

💭 በዓለ ፍልሰታ ወዕርገታ ለማርያም ወፍልሰተ አጽሙ ለሊቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት 💭

ፍልሰታ የግእዝ ቃል ነው፤ #ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ተለየ፣ ሄደ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መሄድን ያመለክታል፡፡
እመቤታችን እንደ ሰው ልማድ ሞትን ትቀምስ ዘንድ ግድ ስለኾነ፤ ጻዕርና ሕማም በሌለበት አሟሟት፤ ዕዝራ በመሰንቆ፥ ዳዊት በበገና እያጫወቷት፤ በተወለደች በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን
#በ48 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ አርፋለች። ሐዋርያትም እንደምታርፍ በመንፈስ ቅዱስ ስለተገለጸላቸው ከያሉበት (ከየሀገረ ስብከታቸው) ወደ መኖሪያ ቤቷ (የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቤት) ተሰባስበው ነበር። ነፍሷ ከሥጋዋ እንደተለየች ሥጋዋን ገንዘውና ሸፍነው ወስደው ለመቅበር ወደ #ጌቴሴማኒ ሲሄዱ አይሁድ ሰምተው መጡና ሐዋርያትን ከበቧቸው።
የአይሁድ ተንኮል አስከሬኗን ከሐዋርያት እጅ ቀምተው በእሳት ለማቃጠል ነበር፤ ይህንንም ማድረግ የፈለጉበት ምክንያት፤ የሐዋርያት ትምህርት (የጌታችን ከሞት መነሳትና ለፍርድ ተመልሶ መምጣት)ከአይሁድ አልፎ ዓለም ሁሉ እያመነበት ስለመጣ እመቤታችንም ተነሥታ ዐርጋለች እያሉ ሐዋርያት ያስተምራሉ በሚል ስጋት ነበር። ‹‹የፈሩት ይነግሣል፥ የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ አበው፤ የእመቤታችን ትንሣኤም ሆነ ዕርገት አይቀሬ ሁኗል። አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋ ለመንጠቅ በሞከሩበት ጊዜም ታውፋኒያ የተባለ ጎልማሳ ሰው በጉልበቱና በድፍረቱ በአይሁድ ዘንድ ተመርጦ የእመቤታችንን ሥጋዋ ያረፈበትን ቃሬዛ ከሐዋርያት ነጥቆ መሬት ላይ ለመጣል ሲሞክር፤ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁሉቱንም እጆቹን ቀንጥሶ (ቆርጦ) ጥሏቸዋል። ነገር ግን ጥፋቱን አውቆ ወዲያው ስለተፀፀተና ይቅርታ ስለጠየቀ በአምላክ ፈቃድ በእመቤታችን አማላጅነት በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት እጆቹ እንደገና ተመልሰውለት የእመቤታችንን እመ አምላክነት (የአምላክ እናት መሆኗ)ና ክብርን ለመመስከር በቅቷል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ በመላእክት ተነጥቆ ከተወሰደ በኋላ በገነት ውስጥ #በዕፀ ሕይወት ሥር መቀመጡ ከዮሐንስ በስተቀር ለሌሎች ሐዋርያት ለጊዜው ምሥጢር ሆኖባቸው ቆይቶ ነበር። ቆየት ብሎ ግን ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ እመቤታችን ሥጋ ነገራቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ለእመቤታችን ካላቸው ክብርና ፍቅር የተነሳ ለምን አልቀበርናትም? ለምንስ የሥጋዋ ምሥጢር ለዮሐንስ ተገልጾ ለኛ ይደበቅብናል? በማለት እያዘኑና እየለ መኑ ከጥር 21 አንስተው ለስድስት ወራት ከዐሥር ቀናት ቆይተዋል። ከዚህም በኋላ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ለ14 ቀናት እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ጠየቁት። በመጨረሻም የነገሩትን የማይረሳ፥ የለመኑትን የማይነሳ ልጇ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ 14 ቀን ሥጋዋን አምጥቶ ስለሰጣቸው፤ ሳይውሉ ሳያድሩ በዕለቱ በጌቴሴማኒ በታላቅ ክብርና ዝማሬ ቀበሯት። በተቀበረችም በ3ኛው ቀን በነሐሴ 16 ከተቀበረችበት መቃብር ተነሥታ ወዲያውኑ በታላቅ ክብር በመላእክት አጃቢነት ወደ ሰማይ ዐርጋለች።

ጥበበኛው ሰሎሞንም “ውዴ እንዲህ ይለኛል ሙሽራዬ ውዴ ሆይ! ተነሺ የእኔ ውብ ሆይ ነዪ አብረን እንሂድ” በማለት አመሣጥሮ የተናገረው በጥበበ እግዚአብሔር ተመርቶ እንደ ክርስቶስ ሆኖ ውዴ ያላት እመቤታችን መሆኗንና ልጇ ተነሥቶ እንደ ዐረገ እሷም መነሣቷንና ማረጓን እንረዳለን። /መሓ.፪፥፲/። እመቤታችን ባረገችበት ጊዜ ሐዋርያው #ቶማስ በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ (ሕንድ) ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ እመቤታችን በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ ተገናኙ። በዚህ ጊዜ ቶማስ ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ አሁንም ደግሞ እርሷን ሳልቀብራት ከትንሣኤዋም ሳልደርስ ቀረሁ ብሎ አዘነ ከደመናው ላይ ሊወድቅም ፈለገ፤ ሆኖም እመቤታችን ዕርገቷን ከእርሱ በቀር ሌሎች አለማየታቸውን ገልጻ አረጋጋችው፤ ዕርገቷንም ለሐዋርያት እንዲነግርና ምልክትና ማስረጃ እንዲሆነው ተገንዛበት የነበረውን ሰበኗን/የከፈን ጨርቅ/ ሰጥታ አሰናበተችው።
ቶማስም መሬት ለይ ወርዶ መቀበሯን፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያላወቀ መስሎ ሐዋርያትን ስለ እመቤታችን ሥጋ ጉዳይ ጠየቃቸው፤ እነርሱም ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቃቸውን፣ ከሱባዔያቸው በኋላ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ሥጋዋን መላእክት አምጥተው እንደሰጧቸውና እንደቀበሯት አስረዱት። እርሱ ግን ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲል ተከራከራቸው። ሐዋርያትም ቶማስን ለማሳመንና ለማሳየት ወደ መቃብሯ ወሰዱት፤ ሆኖም መቃብሯ ባዶ ሆኖ አገኙትና ተደናገጡ፤ በዚህ ጊዜ ቶማስ የሆነውን ሁሉ ገልጾ ለምልክትና ለማረጋገጫ የሰጠችውን ሰበኗን /ተገንዛበት የነበረውን ጨርቅ/ አሳያቸው፤ የራሱን ድርሻም አስቀርቶ አከፋፍሎ ሰጣቸው፤ #ዛሬም_ካህናት ከእጅ መስቀላቸው ጋር የሚይዙት እራፊ ጨርቅ የሚይዙበት ምክንያት ሐዋርያት የተከፋፈሉት የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው።
ሐዋርያትም የዕርገቷን ምሥጢር ካመኑ በኋላ ዕርገቷን ለማየት በዓመቱ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደገና ከነሐሴ 1 ቀን ጀምረው ለ፪ኛ ጊዜ ሁለት ሱባዔ ገቡ፣ እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ በነሐሴ ወር በ16ኛው ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አውጥቷቸው እመቤታችንን አግኝተዋት ከሷ ተባርከው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረዘይት ተመልሰዋል።

በዚህችም ዕለት ከፋርስ ወደ ልዳ የሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍለሰተ አጽም ሆኗል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል ፤ ወለመስቀሉ ክቡር

📜📜📜
📖 ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 📖

💭 ነሐሴ 16

✞✞✞ ዕርገተ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ✞✞✞

ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ ። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ ።
የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው ። እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት ። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ ።
የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ ። ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፀዋት ሁሉም አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት ።
አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት ። በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጁዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች ።
ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው ። እርሱም እንደ አየ እንደ ሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንደ አሳረጓት ነገራቸው ።
ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ ። ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ ። እነሆ እኔ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳትው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ ።
ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሰየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን ።
በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው ። በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት። እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዒ ካህን ሆነ ። እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ ። ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ።
ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው ። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት።
በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው ። መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ ። የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እነሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸውም ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ደንቆች ሥራዎችን አዩ ። እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ ።


+ ጸሎታ ወበረከታ ወምሕረተ ፍቁር ወልዳ ይዕቀበነ ለኵልነ ውሉደ ጥምቀት ለዓለም ወለዓለመ ዓለም አሜን +


✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞
2024/05/26 12:42:07
Back to Top
HTML Embed Code: